Enrolment options
ስለ ስልጠናው
በዚህ የበይነ መረብ ትምህርት ስለሰብአዊ መብቶች መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ፣ ስለሽግግር ፍትሕ ምንነት፣ አስፈላጊነት/ግቦች፤ በሽግግር ፍትሕ እና በሰብአዊ መብቶች መካከል ስላለው ቁርኝት እንዲሁም ቀደም ሲል ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፍትሔ ለመስጠት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ እንዲችሉ የሚያግዟቸውን ክህሎቶች ትማራላችሁ፡፡
ለእናንተ አመቺ በሆነ ሁኔታ እና ጊዜ፣ ካላችሁበት ሆናችሁ ስለሰብአዊ መብቶች እና የሽግግር ፍትሕ መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ ለመማር የሚያስችላችሁ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ባህልን ለመገንባት የበኩላችሁን አስተዋጽዖ ለማድረግ የሰብአዊ መብቶች ውትወታ ክህሎትን ታጎለብታላችሁ፡፡
ስልጠናው የተዘጋጀው ለማን ነው?
ይህ የበይነ መረብ ስልጠና የተዘጋጀው በሰብአዊ መብቶች እና የሽግግር ፍትሕ ጽንሰ ሐሳብ ዙሪያ ቀደም ሲል ምንም ዓይነት የትምህርት ወይም የስልጠና ዕድል ላላገኙ (በጀማሪ ደረጃ/beginner level ላይ ላሉ) ወጣቶች ነው፡፡ በመሆኑም ስለሰብአዊ መብቶች እና የሽግግር ፍትሕ ምንም ዓይነት የትምህርት ወይም የስልጠና ዕድል ያላገኙ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ወጣቶች ይህንን ስልጠና ቢወስዱ በሰብአዊ መብቶች እና የሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የመጀመሪ ደረጃ እውቀት እና ክህሎት ያዳብራሉ፡፡
የስልጠናው ግብ
የዚህ ስልጠና ግብ ወጣቶች በኢትዮጵያ በሚተገበረው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ የላቀ አስተዋጽዖ ማድረግ እንዲችሉ በሰብአዊ መብቶች እና የሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ በማስፋት ዐቅማቸውን ማጎልበት ነው።
የስልጠናው ተሳታፊዎች ከስልጠናው በኋላ፦
ስለሰብአዊ መብቶች ትርጉም፣ ዕሴቶች እና መርሖች መግለጽ ይችላሉ፤
ሰብአዊ መብቶችን በተመለከተ የመንግሥት ግዴታዎችን እንዲሁም የግለሰቦች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ኃላፊነትን መለየት እና ማብራራት ይችላሉ፤
የሰብአዊ መብቶች አፈጻጸም ማዕቀፎችን ማብራራት ይችላሉ፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሲያጋጥሙ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እና የት መሄድ እንዳለባቸው ይለያሉ፤
የሽግግር ፍትሕን ምንነት እና ከሰብአዊ መብቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ማስረዳት ይችላሉ፤
የሽግግር ፍትሕ ከሰብአዊ መብቶች ጋር ያለውን ግንኙነትና ተዛምዶ እንዲሁም እውነትን ከማፈላለግ፣ ዕርቅን፣ የሕግ የበላይነትን እና ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ አንጻር ያለውን ሚና ይተነትናሉ፤
ለሽግግር ፍትሕ ሂደት ውጤታማነት የወጣቶች ተሳትፎ የሚኖረውን ሚና ይገነዘባሉ፤ በሂደቱም ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ፤
የውትወታ ሥራ ክህሎትን ያዳብራሉ፤ በሰብአዊ መብቶች እና የሽግግር ፍትሕ ጉዳዮች ዙሪያ ከሌሎች ግለሰቦች እና ተቋማት ጋር አብረው ይሠራሉ፤
አንኳር አርዕስት፡ ሰብአዊ መብቶች፣ የሽግግር ፍትሕ፣ የወጣቶች ሚና
ስልጠናው የሚወስደው ጊዜ፡ ይህ ስልጠና እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ሰዓታትን በሚፈጁ ሦስት ክፍሎች ተደራጅቶ የቀረበ ሲሆን በጥቅሉ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ ስድስት ሰዓት ይፈልጋል፡፡
የስልጠና የምስክር ወረቀት/ሰርተፍኬት፡ ይህን የበይነ መረብ ትምህርት በተገቢ ሁኔታ ለሚያጠናቅቁ ተሳታፊዎች የተሳትፎ የምስክር ወረቀት የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ስልጠናውን የሚሰጠው ተቋም፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
ስልጠናውን ያዘጋጀው ተቋም፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
ከስልጠናው ጋር በተገናኘ ለመረጃ ልውውጥ የ ኢሜል አድራሻ፡ support@ehrc.org
ፈቃድ/License: CC BY-SA 4.0
ስልጠናው የተጀመረበት ቀን/Date of publication: ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም.